Blogs

የኢሮብ ብሄረሰብ ከ19ኛው ክፍለዘመን እስከ 21ኛ ክፍለዘመን መጀመሪያ የቁልቁለት ጉዞ በጨረፍታ


ከተቆርቃሪ ኢሮቦች/Concerned Irobs

መስከረም 2014 ዓ/ም

የኢሮብ ብሄረሰብ ከ19ኛው ክፍለዘመን እስከ 21ኛ ክፍለዘመን መጀመሪያ የቁልቁለት ጉዞ በጨረፍታ

ከተቆርቃሪ ኢሮቦች/Concerned Irobs መስከረም 2014 ዓ/ም

3ቱ ኢሮብ (ቡክናይቲ ዓረ፣ አድጋዲ ዓረ፣ ሓሳባላ) በማለት ከሚታወቅ የኢሮብ ብሄረሰብ አንድ ኣካል ከሆነው ሓሳባላ የሚወለዱት ደጃዝማች ሱባጋዲስ ትግራይና አሁን ራሷን የቻለች ሀገር ሁና ያለቸው ኤርትራ ያኔ ሲገዙ የነበሩ መሳፍንቶችን አስገብረው ከ1818 እስከ 1831 እንደገዙ የታሪክ መዛግብት ዘግበዉት ያለ ሃቅ ነው። አናሳ ብሄረሰብ ከሆነው ኢሮብ የሚወለዱት ደጃዝማች ሱባጋዲስ መላው የትግራይና የኤርትራ መሳፍንቶችን ለማስገበር ያካሄዱት ብዙ ጦርነት የጀመሩት መጀመሪያ አከባቢያቸው/ዓጋመን ለማስገበር ባካሄዱት ጦርነት ነበር። በዚህ ዓጋመን ለማስገበር ባካሄዱት ጦርነት በሌላው ጦርነቱን በቀላሉ እያሸነፉ የቀጠሉ ሲሆን ኢሮብ ላይ ሲደርሱ ከአድጋዲ ዓረና ሓሳባላ ጎሳዎች ተቃውሞ ባይገጥማቸውም ከቡክናይቲ ዓረ ጎሳና መሪዎቹ (ኦና ፃዕሩና ሓነይታ ኩማኒት) ግን የኢሮብ ራስ ገዝና (Autonomous) የኦና ስርዓታችን ፈርሶ በርስዎ ቀጥተኛ ቁጥጥር ስር መገዛትን አንቀበልም በማለት ተቃውሞ ስለገጠማቸው ተቃውሞዉን በሃይል ወይም በድርድር መፍታት የግድ ይል ነበር። ስለሆነም ደጀዝማች ሱባጋዲስ ለጊዜው ከቡክናይቲ ዓረ መዋጋትን አቁመው በወቅቱ ከሳቸው ጋራ ግኑኝነት ያደርጉ ከነበሩት ኦና ፃዕሩ ጋራ የማዘናጋት ግኑኝነት እያደረጉ ለጦርነቱ በሚገባ መዘጋጀትን መረጡ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ሓነይታ ኩማኒት ደጃዝማች ሱባጋዲስን በጥርጣሬ ዓይን ያዩዋቸው ስለነበረ ከሳቸው ጋራ ምንም ዓይነት ግኑኝነት ሳያደርጉ ራሳቸውን አርቀው በመቀመጥ በበኩላቸው ለሚመጣው ሁሉ ተዘጋጅተው ይጠብቁ ነበር።

ደጃዝማች ሱባጋዲስ የኢሮብ ራስ ገዝ ከጥንት ጀምሮ የኢሮብ ህዝብ ሲተዳደርበት የነበረው የኦና ሥርዓት አፍርሰው የኢሮብን በቁጥጥራቸው ሥር ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ በነበሩበት ወቅት ከኢሮብ ውጭ በዓጋመ ድርቅና ረሃብ ገብቶ ስለነበረ ለኦና ፃዕሩና ሓነይታ ኩማኒት ሠራዊቴ በረሃብ ተጎድቶብኛልና ቀለብ አግዙኝ፣ ይህን ለማድረግ ባትችሉ እንኳን ለአንድ ጊዜም ቢሆን ጥሩ እራት ሰራዊቴን ጋብዙልኝ ብለው ጠየቁ። ሴራው ያልታያቸው ኦና ፃዕሩ የሰራዊቱን የአንድ ጊዜ እራት የመጋባዝ ጥያቄ ሲቀበሉ ከድሮም የደጃዝማች ሱባጋዲስ እንቅስቃሴ በዓይነ ቁራኛ ሲከታተሉ የነበሩ ሓነይታ ኩማኒት ግን አንተ ከፈለግክ ጋብዛቸው እኔ ግን የለሁበትም በማለት ጥሪውን ባለመቀበል በኦና ፃዕሩ ለደጃዝማች ሱባጋዲስ ሰራዊት በተዘጋጀው የእራት ግብጃ ላይ ሳይገኙ ቀሩ። የእራት ግብጃው የቡክናይቲ-ዓረ መሪዎችን (ኦና ፃዕሩና ሓነይታ ኩማኒት) አፍኖ በመያዝ ህዝብን በቀላሉ ለማስገበር የታቀደ ሴራ ስለነበረም ኦና ፃዕሩ በሴራው መሰረት በግብጃው ጊዜ ተይዘው ታሰሩ። ደጃዝማች ሱባጋዲስም ኦና ፃዕሩ ከታስሩ በኋላ ሓነይታ ኩማኒትና የቡክናይቲ ዓረ ህዝብ የትም አይደርስም በማለት የቡክናይቲ ዓረ ህዝብን በሃይል ለማስገበር ጦራቸውን ወደ አከባቢው ላኩ። ይህ ሊሆን እንደምችል ገምተው ቀድመው ተዘጋጅተው ህዝባቸውን አሰባስበው ሲጠባበቁ የነበሩ ሓነይታ ኩማኒት ከተላከው የደጃዝማች ሱባጋዲስ ጦር ጋራ ገጥመው ጦርነቱ በሓነይታ ኩማኒት አሸናፊነት ተጠናቀቀ። የደጃዝማች ሱባጋዲስ የጦር መሪና የተወሰኑ የሰራዊቱ አባላትም ተማረኩ። የጦራቸው መሪና የተወስኑ የሰራዊቱ አባላት መማረካቸውን የሰሙት ደጃዝማች ሱባጋዲስ የጦር መሪያቸውና አብረው የተማረኩ ወታደሮቻቸውን እንዲለቁ ወደ ሓነይታ ኩማኒት መልእክተኛ ላኩ። ሓነይታ ኩማኒት ምርኮኞቹ እንዲለቀቁ ከፈልግክ መጀመሪያ አንተ ኦና ፃዕሩን ልቀቅ፣ ጦርህንም ይዘህ ወደ ቦታህ ተመለስ፣ ከዛ እኔ የጦር መሪህንና ምርኮኞቹን እለቃለሁ ብለው መለሱላቸው። ደጃዝማች ሱባጋዲስ ሓነይታ ኩማኒትና የቡክናይቲ ዓረ ህዝብ ማምረሩን ተረድተው ኦና ፃዕሩን ለቀቁ፣ ሓነይታ ኩማኒትም የደጃዝማች ሱባጋዲስ የጦር መሪና ምርኮኞችን ለቀቁ።

ከጦርነቱ በኋላ ደጃዝማች ሱባጋዲስ የኢሮብ ህዝብን፤ በተለይ ቡክናቲ ዓረን በኃይል ማንበርከክ እንደማይቻል አውቀው መደራደሩ እንደሚሻል አምነው ወደ ኦና ፃዕሩና ሓነይታ ኩማኒት የእንደራደር መልእክት ላኩ። ሁለቱ መሪዎችም ድርድሩን ተቀብለው ሁለቱ ወገኖች ለድርድር ተቀመጡ። የድርድሩ የስምምነት ነጥቦችም ከሞላ ጎደል የምከተሉ ነበሩ፣

1. ኢሮብ ያለማንም ጣልቃ ገብነት ራሱ ባቆየው የአስተዳደር ሥርዓት ራስ-ገዝ ሆኖ እንዲቀጥል፣

2. ደጃዝማች ሱባጋዲስም ሆኑ ሌሎች የኣገርቷ የበላይ ሹመኞች በኢሮብ ራስ ገዝ የውስጥ አስተዳደር ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ፣

3. የኢሮብ ህዝብ በራሱ ባህላዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ የሚመርጣቸው መሪዎቹ በደጃዝማች ሱባጋዲስ እና በሌሎች የኣገርቷ የበላይ አስተዳደርዎች ሙሉ እውቅና እንዲያገኙ፣

4. የኢሮብ ህዝብ ደጃዝማች ሱባጋዲስ የኣከባቢው የበላይ ገዢ መሆናቸውን እውቅና እንዲሰጥ፤

5. እውቅና ለመስጠታቸውን ማረጋገጫ እንዲሆንም ግብር እንዲክፍል፣ የሚሉ ነበሩ፡፡

ይህ ስምምነትም እስከ 1935 ዓ ም የጣሊያን ወረራ በሁሉም የበላይ መንግስታዊ ወኪሎች ተጠብቆ፣ የኢሮብ ራስ-ገዝም ማንም ጣልቃ የማይገባበት አስተዳደር ሆኖ፣ በዓጋመ በሚሾሙ ሹመኞች አማካይነት ከበላይ ባለስልጣኖች ጋራ እየተገናኘ የኢሮብ ህዝብ የኦና ስርዓቱን ይዞ ቀጠለ።

የጣሊያን የ1935 ዓ ም ወረራ ሊጀመር አከባቢ በኢሮብ ህዝብ በቆየው ባህል መሰረት የተመረጡት ኦናዎች፣ ኦና ገብራይ ዕንዳይና ኦና ደስታ ወልደጊዮርግስ ነበሩ። እነዚህ ወኪሎች እንደተመረጡ ብዙ ሳይቆዩ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወሮ ስለተቆጣጠረ፣ በኢሮብ ግዛትም የነዚህ የህዝብ ተመራጮች ውክልና በጣሊያኖች ተሽሮ ጣሊያን የራሱ ወኪል ፊትወራሪ ተሰማ ተስፋይ ሾሙ። የኢሮብ ህዝብም ከብዙ ዘመናት ራሱ በመረጣቸው መሪዎች መተዳደር ወጥቶ በባዕድ በተመደበለት ወኪል እንዲገዛ ተደረገ።

ከ5 ዓመት የጣሊያን ባዕዳዊ አገዛዝ በኋላ ጣሊያን ተሸንፎ ከኢትዮጵያ ሲወጣ አፄ ኃይለስላሴ ከስደት ተመልሰው ስልጣን እንደያዙ፣ ኢትዮጵያን በ14 ጠቃላይ ግዛት በህግ ተሸንሽኖ በየጠቅላይ ግዛቱ ሥርም አውራጃ፣ ወረዳ የሚባል አስተዳደረ እንደተዋቀረ ተደረገ። የኢሮብ ግዛትም ለመጀመሪያ ጊዜ የሶስት ኢሮብ ወረዳ የሚል ኣስተዳደራዊ ስያሜ ተስጥቶት (የራስ ገዝና የኦና ስርዓቱ ተሽሮ) በቀጥታ የወረዳ ገዢ ከላይ ተመደበለት። ለመጀመሪያ ጊዜ በኢሮብ ወረዳ የተመደቡት ወረዳ ገዢም ፊተውራሪ ግደይ የሚባሉ የነበሩ ሆነው እንደተሾሙ ብዙ ሳይቆዩ በአከባቢው በተፈጠረው ግጭት ተገደሉ።

ከፊተውራሪ ግደይ መገደል በኋላ ቀኝ አዝማች እምባየ የሚባሉ በወረዳው ተሾሙ። ወቅቱ በደቡብ ትግራይ ቀዳማይ ወያኔ እየተባለ የሚታወቀው እንቅስቃሴ በአፄ ኃ/ስላሴ መንግስት ተመቶ መላው ትግራይ የነበረው ብረት የሚገፈፍበት ወቅት ስለነበረ በቀኛዝማች እምባየ አማካይነትም የኢሮብ ህዝብም ብረቱ እንዲገፈፍ ተደረገ። ቀኛዝማች እምባየም ወረዳውን ለ4 ዓመት ያህል ጊዜ ገዙ።

ከቀኛዝማች እምባየ በኋላ ባሻይ ብሻኡ የሚባሉ ለወረዳው ገዢነት ቢመደቡም እሳቸው በአከባቢው ብዙ አይቀመጡም ነበርና ህዝቡ በቅርቡ ሆኖ የሚመራው በማጣት ተቸገረ። ይህን በውል የተገነዘቡ፤ ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ የኢሮብ ህዝብ ወደ ችግር ሊገባ መሆኑን ያዩት ሰለቃ ወልዱ ገብራይ (የኦና ገብራይ ዕንዳይ ልጅ)፤ በወቅቱ በመቐለ በመንግስት መስሪያቤት በጥሩ ደሞዝ ሲሰሩ የነበሩ ቢሆንም የመቐለ ስራቸውንና ጥሩ ደሞዛቸውን ትተው በዝቅተኛ ደሞዝ በኢሮብ በምክትል ወረዳ ገዢነት ደረጃ ለመስራት ፈቃደኛ እንደሆኑ ለጠቅላይ ግዛቱ ገዢ ጥያቄ አቀረቡ። ጥያቄያቸውም ተቀባይነት አግኝቶ ሰለቃ ወልዱ የወረዳዋ ምክትል ገዢ ሆነው ተመደቡ። ሰለቃ ወልዱ ከራሱ ከብሄረሰቡ የሚወለዱ፣ ቋንቋና ባህሉን ጠንቅቀው የሚያውቁ በጣም አዋቂና ብልህ ሰው ነበሩ። ለህዝቡ ሁኔታውን በሚገባ አስረድተው ህዝቡን አረጋግተው በቆየው ባህሉ መሰረት ህዝቡን እየመሩ ለማእከላዊ መንግስት መግባት የነበረት ግብር በውቅቱ እያስገቡ እስከ ዕለተ ሞታቸው የኢሮብ ወረዳን አስተዳደሩ። ከሰለቃ ወልዱ ሞት በኋላ ራሱ የቻለ ወረዳነት ተሰርዞ፣ ጉለማክዳ፣ ሱሩኩሶና ኢሮብ አንድ ላይ ተጠቃሎ የዛላምበሳ ወረዳ የሚል ስያሜ ተሰጦት በዚሁ ኣስተዳደር እሰክ የ1966ቱ አቢዮት ቀጠለ።

በ1966ቱ አቢዮት የአጼ ኃይለስላሴ አገዛዝ በህዝባዊ አመጽ ከስልጣ መወገድ በኋላ፤ በ1967 መስከረም 2 ራሱን ጊዚያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በሚል ስም ወታደራዊ ጁንታ ስልጣን ላይ እንደመጣ የኢሮብ ወረዳ የተለያዩ ደርግን በትጥቅ ትግል ለመፋለም ጠመንጃ ያነገቡ ቡድኖች ዋና መናሀሪያ ሆነ። በ1966 አጋማሽ ላይ ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ/ግገሓት የኢሮብ ወረዳ አካል የሆነውን ኣድጋዲ-ዓረን/ማካታ መቀመጫ አድርጎ የትጥቅ ትግል በአከባቢው ጀመረ። በ1964 ዓ/ም በርሊን/ጀርመን ላይ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ህዝቦች አርነት ድርጅት (ኢህአድ) በ1967 ራሱን በፓርቲ ደረጃ በማደራጀት ስሙን ወደ የኢትዮጵያ ህዝብ አቢዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ቀይሮ፤ በነዶክተር ተስፋይ ዳባሳይ፣ ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ኣበራ ዋቅጂራ፣ ክፍሉ ታደሰ፣ ዘርኡ ክሕሸን. . . ወዘተ. ሲመራ የነበረው ድርጅትም ከ1966 መጀመሪያ ጀምሮ ወደ አከባቢው ከራሱ ከኢሮብ የተወለዱ ካድሬዎቹን ወደ አከባቢው ልኮ ድርጅቱን የማስተዋውቅና አባላት የመመልመል ስራ ጀመረ። በኢሮብ ህዝብ ከፈተኛ ተሰሚነትና ክብር የነበረው ዶክተር ተስፋይ ዳባሳይም ከአከባቢው ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች ጋራ እየተገናኘ በአከባቢው ኢህአድ/ኢህአፓን በሚገባ አስተዋወቀ። በውጭ ኣገሮች ሰልጥኖ በኤርትራ በኩል የገባው የኢህአፓ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድንም በ1967 ዓ/ም ላይ ኢሮብ ወረዳ ገብቶ ዋና ቤዙን ዓሲምባ ተራራን አደረገ። የኢህአፓ ትጥቅ ትግል ዓሲምባ እንደገባም ገና በአከባቢው መንቀሳቅስ ከመጀመሩ በፊት መንገድ በመምራትና ከህዝቡ ጋራ በቀላሉ ለመግባባት እንዲረዱ ተልከው የነበሩት እነ ጴጥሮስ ሃይለማሪያም፣ ገረይ ተስፋይ፣ ዳባሳይ ካሕሳይ፣ ደበሱ ካሕሳይ፣ ኩማኒት ወልደገርጊስ፣ ንጉሰ ሙሩቅ፣ ወልዱ ገብራይ፣ ቢኒያም ገብራይ፣ አሰፋ ወልዱ ወዘተ. ቡድኑን ተቀላቀሉ። ልክ ቡድኑ እንቅስቃሴ እንደጀመረ ወደ ትጥቅ ትግሉ ተቀላቅለው የማደራጀት ሥራውን እንዲሰሩ የሚችሉ ተማሪዎችም፤ በወቅቱ ዓዲግራትን ማእከል በማድረግ ኢህአፓን የማደራጀት ስራ ሲመራ በነበረው በገብረእግዚኣብሄር ሃይለሚካኤል/ጋይም አማክይነት ተዘጋጁ።

በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት/ኢዴህ አባላትም ከ1967 መጀመሪያ ጀምሮ በአከባቢው መንቀሳቀስ ጀመሩ።

በ1967 ዓ ም የካቲት ላይ በምዕራብ ትግራይ/ደደቢት በረሃ ትጥቅ ትግል የጀመረው የያኔው ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ/ተሓህት ቡድን በ1968 ሕዳር ላይ ወደ ዓጋመ አውራጃ መጥቶ የማደራጃ ማእከሉን በሱቡሓ ሳዕሲዕ/ማርዋ ላይ በማድረግ፣ በኢሮብ ወረዳም ዋርዓትለ ላይ ማሰልጠኛ ማእከል ነበረው። በመሆኑ፣ በአከባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ቁጥር ወደ 4 አደገ። ተሓህት ወደ አከባቢው እንደመጣ ከግገሓት ጋር በእንዋሃድ ስም ተሰባስበው አብሮ በተኙበት ዛጋብላ በረሃ ተሓህት ሌሊት አባላቱን በመቀስቀስ የግገሓት አባላት ላይ በተኙበት እርምጃ እንዲወስዱ በማዘዝ፣ የሚገደሉትን ገድሎ እጅ የሰጡትን ምርኮኛ በማድረግ ግገሓትን ገና በጨቅላ ዕድሜው ባጭሩ ቀጨው። የኢዴህ አባላትም በኢህአድ/ኢህአፓ ሆነ በተሓህት/ህወሓት ከፍተኛ ክትትል ይደረግባቸው ስለነበረ አከባቢውን ለቀው ወደ ምዕራብ ትግራይ ሄዱ። ስለሆነም ከ1968 መጀመሪያ ጀምሮ በምስራቅ ትግራይ ኢህአፓ/ኢህአሰና ተሓህት ብቻ ቀሩ።

የኢሮብን በተመለከተ በ1968 ተሓህት ላጭር ጊዜ የስልጠና ቦታውን ዋርዓትለ አድርጎ ቢቆይም በኢሮብ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴም ሆነ የማደራጀት ስራ እስከ 1970 ግንቦት አያደርግም ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ በ1968 አጋማሽ ላይ የመሬት ማከፋፈል የጋራ ህግ (ሲሪት) ለመንደፍ ኢህአፓ ለኢሮብ ህዝብ በጠራውና ከመላው ኢሮብ ከ300 በላይ ተወካዮች በተገኙበት የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ ላይ የተሓህት ተወካዮችም ተገኝተው ቀጥሎ የተቀመጠውን የዓላማቸው አንኳር ነጥቦች ለተስብሳቢው ከገለፁ በኋላ፤ ኢሮብን በመወከል አበቶ ዓዶዑማር ሓሊቦ/ጎዒስ መልስ የሰጡት መልስና ከመልሱ በኋላ ተሰብሳቢው የወሰደው እርምጃ ሁለቱን (ህዝቡንና ተሓህት) የሚያገናኝ ዓላማ አለመኖሩን በግልፅ ስለተገነዘቡ ነበር። ስለሆነም መላው ኢሮብ በኢህአፓ/ኢህአሰ ቁጥጥር ሥር ነበር የቆየው።

የተሓህት ተወካይ በቦካለማኮ ለተሰብሳቢው ካደረገው ንግግር አንኳር ነጥቦች፣

1. ስማችን ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ ይባላል፣

2. መሰረታዊ ዓላማችን ባህላችን፣ ቋንቋችንና ትግራዋይ ማንነታችን በአማራ ገዢ መደቦች ስለተጨፈለቅ፣ በቋንቋችን መፃፍ፣ ባህላችን ማሳደግ ስለተነፈግን፣ ትግራዋይ ማንነታችን ስለተረገጠ፣ ባህላችንና በቋንቋችን ለመፃፍና መዳኘት መብታችን ለማስከበር፣ ባጭሩ ሲጠቃለል ከአማራ ገዢ መደብ የሚደርስብንን ብሄራዊ ጭቆና ለማስወገድና የራስችን ዕድል በራሳችን ለመወስን በመታገል ላይ ያለን ልጆቻችሁ ነን።

3. ስለሆነም ከአማራ ብሄራዊ ጭቆና ነፃ ወጥተን የራሳችን ዕድል በራሳችን ለመወሰን በምናደርገው ትግል የናንተ ድጋፍና ተሳትፎ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ የትግራይ ህዝብን ከብሄራዊ ጭቆና ለማላቀቅ በምናደርገው ትግል ከጎናችን እንድትቆሙና እንድትቀላቀሉን ለመጠየቅና ራሳችንን ለማስተወቅ ነው ዛሬ እዚህ በመካከላችሁ የተገኘነው ብሎ ጊዜው እየመሸ ስለነበረ ገለፃዉን ባጭሩ ጨረሰ።

አበቶ ዓዶዑማር ጎዒስ ህዝቡን ወክለው የሰጡት አጭር መልስ፣

1. በመጀመሪያ ስማችሁ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ ከሚባል ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ኢትዮዽያ ቢሆን ጥሩ ነበር።

2. በሁለተኛ ደረጃ አንተ በግልጽ እንዳስቀመጥከው እናንተ የምትታገሉት የተጋሩ ባህልና ቋንቋ በአማራ ገዢ መደቦች ስለተረገጠ በቋንቋችሁ መፃፍን እንድትችሉ፤ ትግራዋይ ማንነታችሁና ባህላችሁን እንድታስከብሩ እንድምትታገሉ በግልፅ ነግረሀናል።

3. በርግጥ እኛ የኢሮብ ብሄረስብ በትግራይ ጠቅላይ ግዛት የምንኖር ህዝብ ነን። ትግራይ መሬታችን ሆኖ በማንነት፣ በባህልና በቋንቋ ከተመጣ ደግሞ ከተጋሩ የተለየ የራሳችን ማንነት/ኢሮብ፣ የራሳችን ቋንቋ/ሳሆ፣ የራሳችን ባህልና ስነልቦና ያለን ራሳችን የቻልን ብሄረሰብ ነን።

4. በቋንቋ፣ ባህል ጭቆናና ረገጣ ከተመጣ ደግሞ የኛ የኢሮብ ህዝብ ቋንቋ (ሳሆ) የሚረገጠው ገና “ቃላይ በዓንቱራ” እንደተሻገርን ኣንታ ዓኳር ሻሃይ፣ ተብለን የምንሰደበውና በቋንቋችንና በባህላችን የምንቋሸሸውና የምንሰደበው በአማራ ሳይሆን በተጋሩ ነው።

5. ካንተ ንግግር እንደሰማነው በማንነት ደረጃ ከታሰበ እኛ ኢሮቦች ከተጋሩ የተለየን የራሳችን ማንነት/ኢሮብ መሆናችን እንኳን አታውቅም ወይም አትቀበልም። ስለሆነ እኛ የኢሮብ ህዝብ እንድንሰማችሁና እንድንደግፋችሁ ከፈለጋችሁ መጀመሪያ በግልጽ ማንነታችን/ኢሮባዊነት ተቀበሉ፣ አክብሩ።

6. ስለ ማንነት፣ የባህልና ቋንቋ ጭቆና ማስወገድ ትግል ይደረግ ከተባለ እኛ የኢሮብ ህዝብ መጀመሪያ መታገል ያለብን ሩቅ ያሉትን አማራን ሳይሆን እዚህ ከጎረቤታችን ከሆኑትና በማንነታችን ከሚጨቁኑን ከተጋሩ/ከናንተ ጋራ ነው መሆን ያለበትና የናንተ ዓላማ ለኛ ለኢሮብ ህዝብ ካለንበት የባህልም፣ የቋንቋም ከሁሉም በላይ ደግሞ የድህነት ጭቆና ለማላቀቅ የሚጠቅመን አይደለም፣ ብለው ንግግራቸውን እንደጨረሱም ተሰብሳቢው የአበቶ ዓዶዑማር ሃሳብ ሃሳባቸው መሆኑ ለማሳየት የተሓህት ልኡካን ቡድን ለቀረበው ሃሳብ የሚሰጠውን መልስ ሳይጠብቅ ከስብሰባው ተነስቶ በመበተን የኢሮብ ህዝብ በኢሮባዊ ማንነቱ ፈፅሞ የማይደራደር መሆኑን በግልፅ አሳያቸው።

የኢሮብ ህዝብ ከ1968-1970 ዓ ም ግንቦት በኢህአፓ/ሰ ስር ሲተዳደር ከቆየ በኋላ በ1970 ግንቦት ላይ ህወሓት ኢህአፓ/ሰ ላይ ጦርነት ከፈተና በአጭር ቀናት ውጊያ ኢህአፓ/ሰ ትግራይን ለቆ ሲወጣ፣ በርካታ የኢሮብ ተወላጆች በኢህአፓ/ሰ ውስጥ ስለነበሩ የተወስኑት ከድርጅቱ ጋራ አብረው ሲወጡ በርከት ያሉ ደግሞ ህዝባችንና መሬታችን ለቀን አንወጣም ብለው እዛው እንደ ተደራጁ ቀሩ። ተሓህት እነዚህ ወገኖችን ማሳደዱን ቀጠለ። በተለያየ ጊዜ በተደረጉ ውጊያዎችም ንጉሰ ተስፋይ/ቡሉፅ፣ ደበሱ ካሓሳይ፣ ተስፋይ ሃይሉ. . . ወዘተን ገደለ። የተቀሩትም ምንም መፈናፈኛ ሲያጡና በነሱ ምክንያት ህዝቡ ብዙ መከራ በተሓህት እየወረደበት መሆኑ በመረዳት ለተሓህት እጅ ከመስጠት ለደርግ እጃቸውን መስጠት መርጠው ለደርግ እጃቸውን ሰጡ። የኢሮብ ወረዳ በተሓህት ቁጥጥር ስር እንደወደቀም በኢህአፓ/ሰ ጊዜ ህዝቡ ራሱ የመረጣቸው የስተዳደር መዋቅሮች በሙሉ እንዲፈርሱ ተደረገ። ህዝቡ የመረጣቸው መሪዎች ከቦታቸው ተነስተው ህወሓት በሚፈልጋቸው ሰዎች እንዲተኩ ተደረገ።

ከ1970 ዓ ም እስከ 1983 ዓ ም ለ13 ዓመታት አብዛኛው ገጠራማው ምስራቅ ትግራይ በህወሓት ብቸኛ ቁጥጥር ስር ቆይታ ወቅትም ገና ታሪክ ለወደፊት ሊዘግባቸው የሚችል ብዙ ግፎች፣ ግድያዎች፣ እስራት፣ የንብረት፣ ከቀየ ማፈናቀል (መንቀል) ውርስ ተፈፀመ። በኢሮብ ወረዳ ደግሞ ህዝቡን የኢህአፓ/ሰ አባል ነህ ወይም ነበርክ በማለት በርካቶች ተገደሉ፣ ታሰሩ፣ ተሰደዱ፣ በቦታው የቀሩም አፋቸውን ዘግተው አጎምብሰው እንዲኖሩ ተደረገ። በዚህ መሰረትም የኢሮብ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ያቆየው ኢሮባዊ ማንነት ከ1970 ዓ ም ጀምሮ ቀስ በቀስ እየተሸረሸረና እየተዳከመ መሄድ ጀመረ።

በ1983 ዓ ም ደርግ ተወግዶ ህወሓት በኢህአዴግ ስም ኢትዮጵያ ወስጥ የመንግስት ስልጣን እንደተቊጣጠረ ትግራይ ክልልን ሲያዋቅር ሌሎች ወደ ኢሮብ መካለል የሚገባቸው ሳሆ ተናጋሪ የኢሮብ ቀበሌዎችን ወደ ትግርኛ ተናጋሪ አካባቢዎች ቢያካልላቸውም የኢሮብ ልዩ ወረዳን አዋቅሯል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ለዘመናት የኢሮብ ህዝብ ማእከል የሆነችውና፤ ከኢሮብ ህዝብ ታሪክና ማንነት ጋራ ከፍተኛ ትርጉምና ቁርኝት የነበራት ታሪካዊ የዓሊተና ከተማ ርእሰ ከተማነትን የህወሓት መሪዎች የህዝቡን አቤቱታ ወደጎን በማለት ወደ ጻውሃን አዛወሩት። ለምን ከ5 ኪሜ በማይበልጥ ርቀት ውስጥ ርእሰ ከተማውን ከዓሳቦል ግድብ ስር ወደሆነችው ዳውሃን መቀየር እንዳስፈለገ የተለያዩ ሰዎች የተለያዩ እሳቤዎችን ቢያቀርቡም፣ ለጊዜው ከዚህ በላይ ወደ ዝርዝሩ መግባት አስፈላጊ አይሆንም። ከዚህ ሌላ የልዩ ወረዳዋ አስተዳዳሪዎችም በቀጥታ በህወሓት የሚሾሙ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹም ቋንቋውን የማይናገሩና ከህዝቡ ባህልና ልምድ ጋር ምንም ትውውቅ ያልነበራቸው ነበሩ። ይባስ ብሎም የልዩ ወረዳው ምክርቤትና የሥራ ቋንቋም ትግርኛ እንዲሆን ተደርጓል።

በ1990 ዓ ም የኤርትራ መንግስት ኢትዮጵያን ሲወር የኤርትራ ወራሪ ጦር ወደ ኢትዮጵያ ከገባባቸው ግንባሮች አንዱ የኢሮብ ልዩ ወረዳ እንደነበረ ይታወቃል። ጦር ወደ አከባቢው ሲገባ ምንም ዓይነት መከላከያ በአከባቢው ስላልነበረ ወደ 50 የሚሆኑ የኢሮብ አርሶ አደሮች በፊታቸው ያገኙትን ጠብመንጃም ጩቤም ሆነ መጥረብያ በማንሳት መላው ህዝባቸውን ወንድ ሴት ሳይሉ ባንዴ በማደራጀት በዓይጋና በአንዳንድ የኣድጋዲ-ዓረ መንደሮች ላይ ከወራሪ ሰራዊት ጋራ በመግጠም ለሶስት ቀን ከባድ ራስን የመከላከል ጦርነት በማካሄድ ጠላትን ወደ መጣበት ለመመለስ ችሎ ነበር፡፡ ይህ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ሥልጠናም ሆነ ሙያ ያልነበረው በእጁ ያገኘውን በመጠቀም በዕለተ እሁድ ባንዴ ከያለበት ተሰባስቦ የኤርትራን መደበኛ ጦር ገትሮ መያዝ ብቻ ሳይሆን እንደገና ተጠናኽሮና ተደራጅቶ ቢመለስም ሰንዓፈ ድረስ አባርሮት ነበር። ከዚህ በመነሳትም ነበር እነዚህን በጀግንነት የተዋደቁትን ጀግኖች “የሰምበት ታጣቂዎች (ዕጡቃት ሰምበት)” የሚል ስያሜ የተሰጣቸው፡፡ ታዲያ ምን ዋጋ አለው የኤርትራ ሰራዊት እንደገና ተደራጅቶ ተመልሶ መጣ፤ የኢሮብ ሚሊሺያም በኢትዮጵያ ሰራዊት በኩል ምንም እርዳታ ስለኣላገኘ መላው አድጋዲ-ዓረ እስከ ዓሊተና ድረስ ያለው ቡክናይቲ-ዓረ መሬት በኤርትራ ሰራዊት ቁጥጥር ስር ወደቀ። በ1992 ዓ ም ሰኔ ወር በኢትዮጵያ ሰራዊት ድባቅ ተመቶ እስከተባረረበት ጊዜ ድረስ ለሁለት ዓመት ያህል የኤርትራ ሰራዊት አከባቢዎችን ተቆጣጥሮት ቆይቷል። በነዚህ የኤርትራ ወራሪ ሰራዊት ሁለት ዓመታት ቆይታ ጊዜም በአከባቢው በመንግስት ሆነ በበጎ አድራጎት ድርጀቶችና በካቶሊክ ቤተክርስትያን ተገንብተው የነበሩና በመገንባት ላይ የነበሩት የልማት ተቋማት፣ ትምህርት ቤቶች የብዙ ግለሰብ ገበሬዎች ቤቶችና ንብረቶች ሳይቀሩ የሚዘረፈው ተዘረፈ፣ መውሰድ ያልቻሉትም እንዲወድም ተደረገ፣ ብዙ ሰው ተገደለ፣ 97 ንጹሃን የኢሮብ አርሶ አደሮችም ታግተው ተወስደው እስከ አሁኗ ሰዓት ደብዛቸው እንደጠፋ ቀርቷል። ዜጎች ታግተው ተወሰዱብኝ ብሎ የሚጠይቅ መንግሥት አለመገኘቱ ብቻ ሳይሆን፣ ቤተ ሰቦቻቸውም ስለታገቱባቸው ቤተ ሰቦቻቸው እንዳያነሱ በመከልከላቸው፣ በውጭ አገር ነዋሪ ኢሮቦች አቤቱታም በመንግሥትም ሆነ በሚመለከታቸው የሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ተገቢ አትኲሮት ሊሰጣቸው ባለመቻሉ የኸው እስከ ዛሬ ለ23 ዓመት ደብዛቸው እንደጠፋ ነው፣ የኢሮብ ብሄረስብም ለ23 ዓመታት መቋጫ ባጣ ሃዘን ውስጥ ይገኛል።

በ1992 ዓ ም የኤርትራ ሰራዊት በኢትዮጵያ ሰራዊት ተሸንፎ ሙሉ በሙሉ ተጠርጎ ወጥቶ በመሸሽ ላይ በነበረበት ወቅት፣ የኤርትራ መንግስት አድርግ የተባለውን ከማድረግ ውጭ ምንም ሌላ አማራጭ ማቅረብ ይችል ባልነበረበት ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ጦርነቱ እንዲቆም አስደርገው ወደ ድርድር በመግባት አልጀርስ ድረስ በመሄድ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት የሆኑ እንደ ባድመና ወደ ግማሽ የሚጠጋ የኢሮብ መሬት ማለት፣ መላው አድጋዲ-ዓረና የተወሰነ የቡክናይቲ-ዓረ ክፍል በአልጀርስ ስምምነት መሰረት በሄግ በተፈረደው የሁለቱ ሃገራት የድንበር ውሳኔ ለኤርትራ እንዲሰጥ ተደረገ። ስለሆነም ዛሬ የኢሮብ ህዝብና መሬቱ፣

1. አንድም ቀን የኤርትራ አካል ሆኖ የማያውቀው፣ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ አካል የነበረው ወደ ግማሽ የሚጠጋ መሬቱ ለኤርትራ በነአቶ መለስ ተሰጥቶበት፣

2. በአከባቢው ምንም ተስፋ የሚሆን ነገር ስለጠፋ ወጣቱ በስደት ወደ ተለያየ አቅጣጫ የተበተነበት፣

3. ኢሮባዊ ማንነት በ’አስሚለሽን’ ለማጥፋት በህወሓት መሪዎች ከ40 ዓመት በላይ በተሰራው እኩይ ሴራ በኢሮባዊ ማንነቱ የማይተማመን (Identity crisis) ውስጥ የገባ፣ ቋንቋዉንና ባህሉን እያጣ ያለ ወጣት ትውልድ የተፈጠረበት፣

4. በሃገር ቤትና በውጭ ዓለም በስደት የሚኖረው የብሄረስቡ ተውላጅ ቁጥር በወረዳው ከሚኖረው ህዝብ ሊብለጥ የምችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ፤ ዛሬ ኢሮብ የሚባል አናሳ ብሄረሰብ ነበር ወደሚባልበት የመጥፋት አቅጣጫ እየተንደረደረ ያለ አናሳ ብሄረሰብ ሆኗል ቢባል ስህተት አይሆንም።

ይህ አልበቃ ብሎ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንድሉት፤ ከጥቅምት መጨረሻ 2013 ዓ/ም ጀምሮ ትግራይ ላይ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የኢሮብ ህዝብ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ የህልውናው አደጋ የባሰ አንጃብቦበት ይገኛል፡፡

ስለዚህ የኢሮብ ህዝብ ራሱን የቻለ ብሄረሰብ ሆኖ የማንነቱ መገለጫዎች የሆኑ ታሪኩ፣ ቋንቋው፣ ስነልቦናው፣ ባህሉና የመሬት ጂኦግራፊያዊ አከላለሉ ተከብሮለት እንዲቀጥል የኢሮብ ተወላጅ በሙሉ የቻለውን ማድረግ የግድ የሆነበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ጠንካራ ማህበረ ኢኮኖሚያዊ መሰረት ያለው፣ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ የተሟሉለትና የተጠበቁለት፣ በዴሞክራሲያዊ ኣስተሳሰብ የዳበረ፣ በኢሮባዊ ማንነቱ የሚኮራና የማይደራደር፣ በሚኖርበት አከባቢ ሁሉ ኢሮባዊ ሥነልቦናዉንና አንድነቱን የጠበቀ የኢሮብ ህዝብ ለማየት፤ እያንዳንዱ ኢሮብ በሚችለው ሁሉ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ይኸው ጥሪ ቀርቧል፡፡

=========//=======

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ፣ ቁጥር አንድ

ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ

መስከረም 2014

ማሳሰቢያ

ይህ ታሪካዊ ተከታታይ መጣጥፍ እኔ/በየነ በግሌ የፃፍኩትና መወሰድ ያለበት ሃላፊነት/ተጠያቂነት ካለ በግሌ እኔ የምጠየቅበት/ሃላፊነት የምወስድበት መሆኑን በቅድሚያ አሳውቃለሁ። ስለሆነም ጥያቄ፣ ሃሳብ፣ አስተያየት፣ ተቃውሞ ካለ ለኔ ለግሌ መቅረብ አለበት እንጂ ከታገልኩበት ድርጅት/ኢህአፓ ሆነ አሁን አባል ከሆንኩበት ኢኣኣ ጋራ ፈፅሞ መያያዝ የለበትም። መጣጥፉን መሰረት በማድረግ ዝርዝር መረጃ የምትፈልጉ ቀጠለው ከሀ እስከ ሐ ከተዘረዘሩት መገናኝ መንገዶች ባመቻችሁ/በፈለጋችሁ (ሀ. ሶሺያል ሚዲያ፣ Beyene G. Tesfu ለ. በጥሪ፣ 004520545658 ፣ ሐ. ኢመይል፣ btesfu45@gmail.com ኮንታክት ካደረጋችሁኝ የማውቀውን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኔን አሳውቃለሁ። የመጣጥፉ አሁን መፃፍ ዋና ዓላማም ታሪክን በታሪክነቱ አውቆ፣ የ60ዎቹ ወጣት ትውልድ የፈፀምነው ስህተት እንዳይደግም ይረዳ እንደሆነ በሚለ መሆኑ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ።

ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ፣ ቁጥር አንድ

ከበየነ ገብራይ/ደንማርክ፤ መስከረም 2014

መግቢያ፣

የኢሮብ ብሄረሰብ ከ19ኛው ክፍለዘመን እስከ 21ኛ ክፍለዘመን መጀመሪያ የቁልቁለት ጉዞ በጨረፍታ በሚል ርእስ በተቆርቃሪ ኢሮቦች/Concerned Irobs በተፃፈው ታሪካዊ መጣጥፍ ውስጥ በ1968 ዓ.ም. የቦካለማኮ/ዓሊተና የ3ቱ ኢሮብ (ቡክናይቲ ዓረ፣ ኣዳጋጺ ዓረ፣ ሓሳባላ) ተወካዮች የተገኙበት ስብሰባ ላይ የተሓህት ተወካይ ስለ ድርጅቱ ማነትና ዓላማ ከገለፀ በኋላ የኢሮብ ህዝብ ምክንያቶቹን በማስቀመጥ የተሓህት ዓላማ እንደማይቀበል ባጭሩ ተቀምቷል። በዚህ ታሪካዊ ስብሰባ የኢሮብ ህዝብ የተሓህት ዓላማ እንደማይደግፍ በግልፅ ስላስቀመጠ፣ በማንነቱ/ኢሮባዊነቱ ፈፅሞ እንደማይደራረድ ግልፅ ስላደረገ ከዛን ጊዜ ጀምሮ በተሓህት አመራር ጥርስ ውስጥ ገባ በሚለው በፅኑ ስለማምን፣ እኔ ራሴ በስብሰባው በአካል ስለነበርኩ፣ ማን ያርዳ የቀበረ፣ ማን ይናገር የነበረ ነውና ስብሰባውና በወቅቱ በአከባቢው ስለነበረው ሁኔታ ለሶሺያል ሚዲያ በሚያምች መንገድ በመከፋፈል በዝርዝር ለማቅረብ እፈልጋለሁ። በቀጥታ ወደ ርእሱ (የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ) ዝርዝር መፃፍ ከመግባቴ በፊት ግን በወቅቱ በአከባቢው (ምስራቅ ዓጋመ አውራጃ) ገጠርማ አከባቢ የነበረ ሁኔታና በወቅቱ በአከባቢው እየተጀመረ ስለነበረው የትጥቅ ትግል እንቅስቃሴ ባጭሩ ማስቀመጥ ነገሩን ከመሰረቱ በሚገባ ለማወቅ ለሚፈልጉና በጉዳዩ መመራመር ለሚፈልግ ምሁራን የተወሰነ መነሻ -ይሰጣል ብዬ ስለማምን የመጀመርያ ክፍል በዚህ ላይ ለማቅረብ እሞክራለሁ።

ሀ. የምስራቃዊ ትግራይ ገጠሮች ፣ ከ1966 አጋማሽ-1968 መጀመሪያ

ከ1966 አጋማሽ-1968 መጀመሪያ የኢሮብ ወረዳን ጨምሮ የምስራቃዊ ዓጋመ ገጠር አከባቢ (ኢሮብ፣ ጉለማክዳ፣ ሱቡሓ ሳዕሲዕና የተወሰነ ጋንታ አፈሹም) የመንግስት መዋቅር ፈርሶ ህዝቡ አስተዳደራዊ ችግሮች ሲገጥሙት አቤት የሚልባቸው መንግሥታዊ መዋቅሮች አልነበሩም። አከባቢዎቹ በተለያዩ መንግስትን በትጥቅ ለመፋለም እየተዘጋጁ የነበሩ ኃይሎች እንቅስቃሴ ጀምረዉበት የነበረ ቢሆንም ከ1966 አጋማሽ እስከ 1967 መጀመሪያ አጋማሽ ሌብነት በከፍተኛ ደረጃ እየተስፋፋበት የነበረ አከባቢ ነበር። በወቅቱ በአከባቢው ትጥቅ ትግል ለመጀመር ይንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች በቀደም ተከተል፣ 1. ከ1964- 1967 ነሓሴ ድረስ የኢትዮጵያ ህዝቦች አርነት ድርጅት/ኢህአድ በ1967 ነሓሴ ላይ ራሱን ወደ ፓርቲ ደረጃ አሳድጎ ስሙን ወደ ኢትዮጵያ ህዝባዊ አቢዮታዊ ፓርቲ/ኢህአፓ የቀየረው ቡድን ካድሬዎቹን (ህዝብ መካከል ህዝቡን መስለው የሚሰሩ ውሱን አባላት) ከ1966 መጀመሪያ ጀምሮ መድቦ በአከባቢው (በተለይ በኢሮብ) በዓዲግራት ከተማ ያንቀሳቅስ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ በውጭ በዋናነት በሶሪያ በPLO እርዳታ ያሰለጠናቸው ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድኑን የየካቲት አቢዮት ከመፈንዳቱ በፊት ለማስገባት ቡድኑ 1966 መባቻ ላይ ሳሕል/ኤርትራ ቢያስገባም በህግሓኤ/ሻዕቢያ አመራር ማጓተት ምክንያት በ1967 አጋማሽ ላይ አስገብቶ ‘ቤይዙ’ን ዓሲምባ በኢሮብ በማድረግ በአከባቢው እንቅስቃሴ ጀመረ። 2. ግንባር ገድሊ ሓርነት ትግራይ/ግገሓት በ1966 አጋማሽ ላይ ቤዙን ማካታ/ኣድጋጺዓረ በማድረግ በአከባቢው መንቀሳቀስ ጀመረ። 3.የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ህብረት/ኢዴህ በ1967 መጀመሪያ ጀምሮ በአከባቢው መንቀሳቀስ ጀመረ። 4. ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ/ተሓህት ትጥቅ ትግሉን የጀመረው ምዕራብ ትግራይ ሽረ/ደደቢት በ1967 አጋማሽ ሲሆን ከ1968 ሕዳር ጀምሮ ወደ አከባቢው መጥቶ ቤዙን ማርዋ/ሳዕሲዕ አድርጎ መንቀሳቀስ ጀመረ።

ግገሓት ገና ትጥቅ ትግሉን የጀመረበት ሁለተኛ ዓመት ልደቱን ሳያከብር በእንዋሃድ ሴራ በህወሓት ዛጋብላ በሚባል በርሃ ተመቶ ዕድሜው ባጭሩ ተቀጨ። ስለ ግገሓት ከትግል ሜዳ መጥፋት፣ ድርጅቱን ያጠፋው ተሓሕት/ህወሓት ከነገረን ውጭ በትክክል ለምን በዛ መልክ ክትግል እንዲወገድ ተደረገ በሚለው አቶ አስገደ ገ/ስላሴ ጋህዲ በሚል መፅሃፉ ካሰፈረው ውጭ ከሌላ ነፃ ምንጭ የማዳመጥ ዕድል አልገጠመኝም። የኢዴህ አባላትም በተሓሕትም በኢህአፓም/ሰም ጫና ይበዛባቸው ስለነበረ በተለይ ከግገሓት መመታት በኋላ ለነሱም እንደማይቀርላቸው በመረዳት ከአጭር ጊዜ (ወደ አንድ ዓመት) ቆይታ በኋላ ምስራቅ ትግራይን ለቀው ወደ ምዕራብ ትግራይ ጠቅልለው ስለሄዱ ከ1968 የመጀመሪያ አጋማሽ በኋላ በምሥራቅ ትግራይ የቀሩት ተፋላሚ ድርጅቶች ኢህአፓ/ሰና ያኔ ተሓህት ከ1972 በኋላ ህወሓት ብቻ ሆነው ቀሩ።

የምስራቅ ዓጋመ ህዝብ 4ቱንም ድርጅቶች በእኩል ዓይን በማየት ሁሉንም እኩል ያስተናግድና ያዳምጥ ነበር። ይህም የሆነው፣ አራቱም ድርጅቶች የተለያየ ዓላማ የነበራቸው ቢሆኑም፣ ከአብራኩ የተፈጠሩ ልጆች ስለነበሩ ነበር።። የድርጅቶቹ አባላት ይዘት ሲታይ፣ የሶስቱ (ተሓህት፣ ግገሓትና ኢዴህ) በወቅቱ የነበሩ አባላት በሙሉ ተጋሩ የነበሩ ሲሆን ከኢህአፓ/ሰ አባላትም በወቅቱ ከነበሩት 2/3ኛ የሚሆኑት ከትግራይ ነበሩ። የወቅቱ የድርጅቶቹ መሪዎች የነበሩ ደግሞ፣ ግገሓት በመምህር ዮሃንስ ተክለሃይማኖት ይመራ ነበር። ኢዴህ በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ይመራ ነበር። ኢህአፓ/ሰ በብርሃነ መስቀል ረዳ ይመራ ነበር። ተሓህት በበሪሁ በርሀ/አረጋዊ ይመራ ነበር። ሌላም በአመራር ደረጃ የነበሩ ሆነ ተራ አባላቱ ከዓላማ ልዩነት ውጭ በትግራዋይነት የማይበላለጡ እኩል ተጋሩ መሆናቸው ህዝቡ በሚገባ ያውቅ ነበር። ያኔ ህዝቡ እንደ ዛሬ በአንድ ድርጅት/በህወሓት ብቸኛ ፈላጭ ቆራጭነት ቁጥጥር ሥር ስላልነበረ በነፃነት የሁሉንም ሓሳብ የማዳመጥ መብቱ አልተነጠቀም ነበር። የየድርጅቱን ዓላማና ራእይ አዳምጦ ይበጀኛል የሚለውን ለመደገፍ፣ የማይመስለው ሃሳብ ሲነሳ ለመቃወም፣ የፈለገውን ድርጅት ለመደገፍ ሆነ ለመቀላቀል፣ የማይደግፈውን ድርጅት ወይም ሃሳብ ለምን እንደማይደግፈው በግልፅ ለመናገር ብቃት፣ድፍረት፣ ዝግጁነትም ነበረው፣ በግልፅም ይናገር ነበር።

ከላይ ባጭሩ እንዳስቀመጥኩት ግገሓት በተሓህት በተወሰደበት እርምጃ፣ ኢዴህ ደግሞ በኢሕአፓና ተሓህት ፖለቲካዊ ተጽእኖ አከባቢውን በመልቀቅ በህዝቡ የነበራቸው ተቀባይነት ሆነ ሊፈጥሩት ይችሉ የነበረውን ተጽእኖ ብዙ ሳይታወቅ ባጭር እንደተቀጩ ቀሩ። ግገሓት ዓላማውን ህዝቡ ውስጥ ብዙ አሰርፆ ያልነበረ ቢሆንም በዛጋብላ በርሃ በተሓህት መመታቱ፣ በበረሃው በጅምላ መቃብር የተቀበሩ ጉድጓዱ ጥልቅ ስላለነበረ ፅሕሪያ የሚባል አራዊት ጉዷዱን ከፍቶ አከባቢው ስለ ሸተተ፣ የሞኖክሶይቶ እረኞች አይተው ለዝቡ ነግረው ህዝቡ እንደገና ስለቀበረ መገደላቸ በጉለማክዳ ህዝብ በሚገባ ይታወቅ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ከተገደሉት ውስጥ በአከባቢው በሚገባ የሚታወቁት የባራምባራስ ገ/መስቀል/ቀፅቀፂያ ልጅ የማነ ገ/መስቀል ስለነበረ፣ ግዲያውን ካመለጡት ደግሞ እንደ ኃይለሚካኤል አባጎበዝ፣ ደጀን ተሰማ፣ ደስታ ተስፋይ፣ ዓነቶቹ የአክባቢው ተወላጆችና በብዙዎች የሚታወቁ ስለነበሩ ስለ ድርጅቱ አጠፋፍ በስፋት ያወራ ነበር፣ የተሓሕት ድርጊትም ህዝቡን አስቆጥቶና አሳዝኖትም ነበር።

ከ1968 መጀመሪያ ጀምሮ አከባቢው ኢህአፓ/ሰና ተሓህት ሙሉ ቁጥጥር ሥር ገባ። ሁለቱም ድርጅቶች ህዝብን የሚያስተምሩና የሚያደራጁ ካድሬዎቻቸውን (ብዙሃን ድርጅት እየተባሉ ሲጠሩ የነበሩ) በመመደብ በሁሉም የገጠር አከባቢዎች በስፋት ይንቀሳቀሱና ደጋፊዎቻቸው/አባላት ይመለምሉ ነበር። እንዲሁም በወቅቱ በጋንታ ደረጃ ተደራጅቶ የነበረ ሠራዊታቸው (አንድ ጋንታ ማለት ከ20-30 ሰው የሚይዝ) በሚያርፉባቸው መንደሮች ህዝቡን በመሰብሰብ ዓላማቸውን ለህዝቡ በስፋት ያስተምሩ ነበር። ስለሆነም ህዝቡ ስለ ሁለቱ ድርጅቶች ማንነትና ዓላማ ገና ከ1968 አጋማሽ ጀምሮ በሚገባ እንዲያውቅ ተደርጎ ነበር።

ኢህአፓ/ሰ ዓብይ ቅራኔ (በጠምንጃ እንጂ በውይይት የማይፈታ ቅራኔ) ሲፈርጅ፣ በገጂዎች (መሳፍንቶች፣ አቀባባይ ከበርቲዎች) እና በጭቁን የኢትዮጵያ ህዝቦች መካክለ ያለው ቅራኔ አድርጎ፣ ደርግን ስልጣን ላይ እንደመጣ የጭቁኖች ወገን ሊሆን ይችላል የሚል ግምት የነበረው ቢሆንም የደርግ ትክክልኛ ፋሽስታዊ ባህሪው ገና ስልጣን በያዘ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ 60ዎቹን የድሮ ሚንስትሮች በመረሸን ስለጀመረ፣ ገና በአዋጅ ስልጣን እንደያዘ በወቅቱ የነበረው ሰላማዊ ትግልና እንቅስቃሴ ሁሉ በአዋጅ ከልክሎ ማሰር፣ መግደል ስለጀመረ ደርግንም በዋና ጠላትነት ደረጃ ፈርጆ ሁለገብ ህብረ ብሄራዉ ትግል በ1968 ጀመረ። ተሓሕት ዓብይ ቅራኔ ስፈርጅ፣ ዓብይ ቅራኔ (በጠምንጃ እንጂ በውይይት የማይፈታ ቅራኔ) በገጂው የአማራ ብሄርና በተቀሩት የኢትዮጵያ ጭቁን ብሄር/ብሄረሰቦች መካከል ያለ ቅራኔ ነው ብሎ ፈርጆ፣ መካሄድ ያለበት ሁለገብ ትግል ፀረ የአማራ ሆኖ በየብሄሩ የሚካሄድ ትግል መሆን አለበት በማለት ነበር ትግሉን የጀመረው።

ሁለቱ ድርጅቶች እርስ በርስ መፈረጃጀት፣ ማጥላላት ስም መሰጣጠት የጀመሩት ገና ከጅምሩ ነበር። ተሓህት የኢህአፓ/ሰ የአንድ ብሄር (አማራ) ተወላጆች ድርጅት አድርጎ በማስቀመጥ፣ ትምክህተኛ፣ የብሄር/ብሄረበሰብ ጥያቄ/ጭቁና የማይቀበል፣ # ናይ ዓባይ ኢትዮጵያ ናፋቒ/ተሓላቒ# የታላቋ ኢትዮጵያ ናፋቂና ጠበቃ፣ ብሎ በመፈረጅ ከኢህአፓ/ሰ ጋር ተሰልፈው ለነበሩ ተጋሩ ደግሞ #ኮራኹር አምሓራ# (የአማራ ቡችሎች) ብለው ይፈርጃቸው ነበረ። ኢህአፓ/ሰ እንደ ድርጅት ተሓህትን፣ በዴሞክራሲያዊ የብሄር ጥያቄ ስም የሚነግድ ለግል ጥቅምና ስልጣን የቆመ የጠባብ ብሄረተኛ ስብስብ ብሎ ይፈርጀው ነበር። በኢህአፓ/ሰ ተሰልፈው ሲታገሉ የነበሩ ተጋሩ ተሓህትን ጠባቦች በትግርኛ # ካብ ዓይኒ ዑንቂ ዝፀበብኩም ፀበብቲ# ይሉዋቸው ነበር። በድርጅት ደረጃ የነበረው ጥላቻ እንዳለ ሆኖ በኢህአፓ/ሰ ውስጥ በነበሩ ተጋሩና በህወሓት አባላት መካከል የነበረው ጥላቻ ግን የላቀ ነበር። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎቹ ከትምህርትቤት ጀምሮ በሚገባ የሚተዋወቁ አንዳንዶቹም ወደ ትግል ሜዳ ከመውጣታቸው በፊት ጥሩ ጓደኞች የነበሩ ስለነበረ፣ በተለይ በኢህአህአፓ/ሰ ውስጥ የተሰለፉት የአማራ ቡችሎች የሚለው ስድብና እነሱ/ተሓህቶች ለትግራይ አሳቢ እነሱ/ በኢህአፓ/ሰ የተሰለፉ ደግሞ ለትግራይ ምንም የማያስቡ ትግራይን ውጭ ያደረገች ታላቋ ኢትዮጵያ ህልመኞች ተደረገው መቀመጥ በጣም ያማቸው ነበር።

ተሓህት ኢህአፓን በብሄር ጥያቄ ላይ ግልፅ አቋም የሌለው የታላቋ ኢትዮጵያ ናፋቂ ድርጅት ነው ብሎ ፈርጆ ቢቀሰቅስበትም ኢህአፓ የብሄር ጥያቄን በፖለቲካ ፕሮግራሙ ካስቀመጣቸው 9ኙ ዓበይት ነጥቦች አንዱ አድርጎ አስቀምጦ ጥያቄው ለአንዲት ዴሞክራሲያዊትና ሉዓላዊት ኢትዮጵያ ለመመስረት በሚደረገ ህብረብሄራዊ የመደብ ትግል ስር ሊፈታ ይችላል የሚል ግልፅ አቋም ነበረው። ኢህአፓ በብሄር ጥያቄ ላይ ያኔ የነበረው አቋም ለማታውቁ ድርጅቱ መሰረታዊ አቋሞቹን ለህዝብ ይፋ ያደርግበት የነበረው በድርጅቱ ልሳን በዴሞክራሲያ “ዴሞክራሲና የብሄር ጥያቄ” በሚል ርእስ ጥር 7 ቀን 1967 የወጣውን በያ ትውልድ ድረ-ገፅ በመግባት ቀጥሎ በተቀመጠው ሊንክ መሰረት ማግኘት ይቻላል።

ከላይ በሰፈረው ሊንክ ሙሉውን በአደፍርስ ተባዝቶ የተሰራጨውን ሰነድ ለማንበብ አስቸጋሪ ለሆነባችሁ የአቋሞቹን አንኳር አንኳር ነጥቦች እንደሚከተለው ሰፍሯል፣

#የአንድ ሶሺያሊስት እውነተኝነትና ትክክለኛነት የሚፈተነው የማያወላውል ዴሞክራሲያዊነቱ ከሚረጋገጥባቸው አንዱ

በብሄር ጥያቄ ላይ በሚወስደው አቋም መሆኑ ከሳይንሳዊ ሶሺያሊዝም አስተማሪዎች አንዱ አስተምሯል። ትክክል በመሆኑም

ይህ ሃሳብ ተቀብለናል፣ አቋምችንም አሳውቀናል፣ እንደገና ማሳወቅ ካስፈለገም፣

1. በብሄሮች መካከል የሚደረገው የኢኮኖሚ፣ የባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት . . . ወዘተ. መበላለጥ በጥብቅ እየተቃወምን የማናቸው ብሄር ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት. . . ወዘተ. ከማናቸው ሌላ ባህል፣ ቋንቋ፣ እምነት. . .ወዘተ. እኩል መታየት አለበት።

2. የብሄር እኩልነት በቃላት ብቻ የሚለፈፍ ሳይሆን በገቢርም መታየት አለበት፣ የኸውም ማናቸውም ብሄር አንዳችም የውጭ ተጽዕኖ ሳይደረግበት የራሱ ባህል፣ ቋንቋ እምነት ሊያስፋፋ ይችላል። ትምህርት፣ ፍርድ፣ አስተዳደርን. . .ወዘተ. በራሱ ቋንቋ እንዲያካሂድ ተደርጎ ይህ መብቱ በህግ ሊጸድቅ ይገባል።

3. ማናቸውም ብሄር የራሱን ዕድል የመወሰን መብት ሲኖረው ከሌሎች ብሄሮች ጋራ በፍጹም መዋሃድ፣ በኢኮኖሚ፣ የውስጥ አስተዳደር መብት በፈደረሽን ወይም በሌላ መንገድ የሚተሳሰረው በራሱ ፈቃድ ብቻ ነው። ይህ የራሱን ዕድል የመወሰን መበት ተገንጥሎ የራሱ አስተዳደር የመመስረት መብትን ያጠቃልላል። ፈቅዶ ከመዋሃድ ሌላ በሃይል፣ በማስፈራራት፣ በዛቻ፣ በማስገደድና በሌሎች በማናቸውም ጸረ ዴሞክራሲ ዘዴዎች የሚደረገው መዋሃድና አንድነት አንደግፍም።

4. ምን ጊዜም ቢሆን ከብሄር ትግል ይልቅ ለመደብ ትግል ቅድሚያ በመስጠት፣ በቀላሉ የንኡስ ከበርቴ መጠቀሚያ ሊሆን የምችለውን የብሄር ትግል መደባዊ መልክ በማስያዝ ወዛደራዊ የመደብ ትግል ለማድረግ መጣር አለብን።

5. የራስን ዕድል የመወሰኑ ተግባር የሚካሄደው ሁኔታው በሚፈቅደው በተለመደው ዴሞክራሲያዊ መንገድ/ወካይ ፓርላማ ፣ ረፈረንደም/አንድ ሰው አንድ ድምጽ ይዞ በመምረጥ. . . ወዘተ. ብቻ ነው። ባጭሩ ሞላው የብሄሩ ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተወካይ የራሱን ዕድል ለመወሰን ድምጽ ከሰጠ በኋላ ነው።# የሚሉት ዋና ዋና ነጥቦቹ ነበሩ።

በነዚህ የድርጅቱ መሰረታዊ የአቋም ነጥቦች መሰረት ኢህአፓ/ሰ ከ1967 ግንቦት እስከ 1968 አጋማሽ በነበረው ወደ 10 ወር ያህል ጊዜ በአከባቢው ያለ ተቃናቃኝ (ተሓህት በወቅቱ በአከባቢ ምንም እንስቃሴ አልነበረውም) ትጥቅ ትግል ጀማሪ አባላቱንና ዓላማውን ለማስተዋውቅ ጥሩ ዕድል አገኘ። ያለ ማጋነን ኢህአፓ/ሰ ትጥቅ ትግል ጀማሪ ቡድን ውስጥ ለህዝቡ በራሱ ቋንቋ/ትግርኛ ትምህርት ሊሰጡ የምችሉ ብቃት የነበራቸው አባላት ስለነበሩት ህዝቡ ድርጅቱን ገና ከጅምሩ በጥሩ ሁኔታ ተቀብሎትና ደግፎት ነበር። ለዚህ ማስረጃው ደግሞ በምስራቅ ትግራይ ከ1968 መጀመሪያ አጋማሽ ጀምሮ ተፈጥሮ የነበረው የአስተዳደር ክፍተት ለማሟላት ከራሱ ከህዝቡ የሚመረጥ አስተዳደርና የገበሬ ማህበራት በምስራቃዊ ትግራይ ከአንድ ከሰበያ ቁሸት ውጭ የተመሰረቱት በኢህአፓ/ሰ ነበር። በምስራቅ ትግራይ የመጀመሪያ የመሬት ማከፋፈል ስራም ከሰበያ ውጭ የተካሄደው በኢአፓ/ሰ ነበር። ስለሆነም፣ በምስራቃዊ ዓጋመና ሰራዊቱ ሲንቀሳቀስበት በነበረው የዓድዋ፣ ክልተ አውላዕሎ ወረዳዎች ገጠራማ አከባቢ በህዝቡ ኢህአፓ/ሰ ከተሓህት የበለጠ ድጋፍና ተቅባይነት ነበረው፣ ያኔ ከአከባቢው ወደ ኢህአፓ/ሰ የተቀላቀሉትና ለመቀላቀል ይፈልጉ የነበሩ ወደ ተሓሕት ሲቀላቀሉ ከነበሩ ይበልጡ ነበር።

ኢሮብ ወረዳ በጅዮግራፊያዊ አቀማመጥ በምስራቅ ትግራይ የሚመደብ ሲሆን የኢሮብ ብሄረሰብ ከጥንት ጀምሮ ራሱን፣ ራሱ የቻለ ብሄረሰብ አድርጎ የሚያይ በቁጥር አናሳ የአስተሳሰብና ማንነት ጉዳይ ሲነሳ ግን ራሱን እንደ ትልቅ አድርጎ የሚያስቀምጥ፣ በትግራይ ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ ፖለቲከኖች የወጡበት ብሄረሰብ ነበር። ለዚህ ማስረጃ Suba Hais በሚል የብእር ስም በእንግልዝኛ ከተፃፈውና www.advocacy.irobpeople.org ከሚገኘው ስለ ኢሮብ ህዝብ ሰፊ መረጃ ከያዘው ጠቃሚ አርትክል ቀጥሎ የተቀመጠውን መመልከት ይቻላል። እጠቅሳለሁ፣ “Irob, despite its physical location by the border area, in essence, is a core part of Tigray. In fact, most Tigrayan leaders who played important roles in regional and national politics were fully or partly Irob descendants. Just to mention a few randomly: Sum ‘Agame Woldu, Dej Subagadis, Emperor Yohannes IV, Iteghie Denqnesh, Ras Sebhat, Shum Agame Desta, Ras Araya, Dej. Hagos, Dej. Derso, Dej. Maru, Dej. Tedla Abaguben, Shum Agame Aregawi, Dej. Belay Weldiye, Dej. Kassa, Azmach Ayele, Dej. Gebreselassie, Dej. Zewde Gebreselassie, Betweded Hailemariam, Fitwrari Tessema Tesfay, Major Biru Sebhat, Colonel Gebray Gebrezghi, Colonel Adhanom, Colonel Abraha Adagis (Yeogaden Anbesa), Dr. Abraham Demoz, Dr. Tesfay Debessay etc.”

ያኔ (1968) የነበረው የኢሮብ ህዝብ በኢሮባዊ ማንነቱ ፈፅሞ የማይደራደር፣ ብሄራዊ ጭቆና ከተነሳ የኢሮብ አናሳ ብሄረሰብ ጨቋኞች ተጋሩ ናቸው ብሎ የሚያምን፣ ለዘመናት የነበረው ራስ ገዝ የኦና ስርዓት በአፄ ኃ/ስላሴ ቢነጠቅም ገና በኦና ስርዓት ጊዜ የነበረው አስተሳሰብ፣ ባህል፣ ስነልቦናና ኢሮባዊ ማንነትና አንድነቱ እንዳለ ይዞ የነበረ ህዝብ ስለነበረ የትሓህት ዓላማ ሊቀበል የምችልበት ሁኔታ ሆነ ምክንያት አልነበረም። ስለሆነም ወረዳው ኢህአፓ/ሰ ጠቅልሎ ከትግራይ እስክወጣበት 1970 ግንቦት (ከ1967-1970 ወደ 3 ዓመት) በኢህአፓ/ሰ ቁጥጥር ስር ነበር። ገና ከጅምሩም ብዙ የኢሮብ ወጣቶች ኢህአፓ/ሰን ተቀላቅለው ነበር፣ ህዝቡም ኢአፓ/ሰን ይደግፍ ነበር።

በሚቀጥለው #የቦካለማኮ/ዓሊተና ስብሰባ በተመለከተ፣ ስብሰባው መጥራት ለምን አስፈለገ፣ ስብሰባውን የጠራውስ ማን ነበር፣ በሚል ርእስ ዝርዝር ይዤላችሁ እቀርባለሁ።

የነገ ሰው ይበለን።